ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በክልሉ በተፈጠረው ሁኔታ ተቋሙን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና መርሃ ግብር አካሄደ

ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በክልሉ በተፈጠረው ሁኔታ ምክንያት ተቋሙ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በመቋቋም፣ የዩኒቨርሲቲውን ቀጣይነት ለመጠበቅና ዳግም ወደ መደበኛ ሥራ እንዲመለስ የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን ላበረከቱ አካላት የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

የመርሃ ግብሩን በይፋ የከፈቱት የአካዳሚክ፣ ምርምርና ማኅበረሰባዊ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ሃፍታይ ገብረዮሱስ ሲሆኑ፣ በንግግራቸውም በአስቸጋሪው ወቅት የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ያሳየው መተሳሰብ፣ ደግነት፣ አብሮነትና አንድነት የጋራ ኃላፊነትንና ለተቋሙ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ያጋጠሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ዳግም ወደ ሥራ መመለሱ የማኅበረሰቡን ትብብርና የጋራ ጥረት የሚያሳይ መሆኑንም አስረድተዋል። በቀጣይም የተጀመሩ ጥረቶችን ማጠናከርና የተቋሙን እድገት ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዕለቱ የሥነ ልቦና መምህርና የኮግኒቲቭ ሳይኮሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ተክለብርሃን በርሀ ስለ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት (Trauma) ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሰፊ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም የጦርነትና የግጭት ሁኔታዎች በግለሰቦችና በማኅበረሰብ ላይ ሊያሳድሩ ስለሚችሉት የሥነ ልቦና ተጽዕኖ፣ እንዲሁም ለመልሶ ማገገም የሚያግዙ የሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፎች አስፈላጊነት ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሥነ ልቦና መምህሩ ተባባሪ ፕሮፌሰር አሰፋ ተስፋይ በጦርነት ወቅት የነበሩ ሁኔታዎችንና በማኅበረሰቡ ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ በተመለከተ ትንታኔና ማብራሪያ አቅርበዋል።

በመድረኩ የአካባቢውን አገር ሽማግሌዎች ወክለው የተገኙት አቶ ዓለም ቢሆን በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በተጋጠሙት ፈተናዎች ውስጥ በጽናት በመቆየት የጀመረውን ሥራ ማስቀጠሉን አድንቀዋል። በቀጣይም ይህንኑ ጥረት እንዲያጠናክር የማበረታቻ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳድርና ልማት ም/ፕሬዝዳንት እና የፕሬዚዳንት ተወካይ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጽጋብ አረጋዊ፣ በክልሉ በተፈጠረው ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው ካለበት አካባቢ አንጻር ለተለያዩ ተጋላጭነቶች የተጋለጠ በመሆኑ ተቋሙ እንዳይጎዳ ከፍተኛ ስጋት እንደነበራቸው ገልጸዋል። ሆኖም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር ተቋሙን በመጠበቅ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስበት ማድረጉን አብራርተዋል። ተቋሙን ለመጠበቅ የታየው ጽናትና አንድነት የዩኒቨርሲቲውን ራዕይ ለማሳካት በሚደረገው ቀጣይ ጥረትም እንደሚደገም እምነታቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በአስቸጋሪው ወቅት ዩኒቨርሲቲው ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስበት በመጠበቅና የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን በማበርከት ለተባበሩ አካላት የምስጋና ሰርተፊኬት የማበርከት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል። በሥነ ሥርዓቱም የአገር ሽማግሌዎችና የንግድ ማኅበረሰቡ ተወካዮች ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ሰርተፊኬቶቹን አበርክተዋል።