የመውጫ ፈተና በሰላምና በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ
“ፈተናው ያለምንም የቴክኒክ እና የፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁ እንደ ተቋም ትልቅ ኩራት ነው።”
ዶ/ር ገብረሚካኤል ወልደገብርኤል፣ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት
በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲሰጥ የቆየው የመውጫ ፈተና (Exit Exam) በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲም በሰላምና በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። የፈተናውን መጠናቀቅ ተከትሎ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገብረሚካኤል ወልደገብርኤል የምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ በመልዕክታቸው ለፈተናው ዝግጅት ከተለያዩ ክፍሎች የተውጣጣ አብይ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከዝግጅት ሥራ ጀምሮ ፈተናው እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉንና ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር እና የቴክኒክ መስተጓጎል በሰላም መጠናቀቁ ለዩኒቨርሲቲው ትልቅ ስኬትና ኩራት መሆኑን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም በፈተናው ሂደት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን ገልጸዋል። በተለይም ለኢትዮ ቴሌኮም፣ ለከተማው ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለዩኒቨርሲቲው የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት፣ ለሰላምና ደህንነት አካላት፣ እንዲሁም ለአመራሩና ለመላው ባለሙያ ሠራተኞች ዩኒቨርሲቲው ከልብ የመነጨ ምስጋናና ክብር እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።
ከሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚካሄደው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በቂ ዝግጅት መደረጉን ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ፣ የመውጫ ፈተናውን የወሰዱ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም በዓዲግራትና በአካባቢው የሚገኙ በኦንላይን ፈተናቸውን የሚወስዱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በፈተናው ወቅት የቴክኒክ ችግር እንዳያጋጥማቸው የተለያዩ የልምምድና የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፣ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የፈተና ማዕከል ኃላፊ ረ/ፕሮፌሰር ታደሰ ብርሃነ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ከፍተኛ አቅምና ልምድ በመጠቀም በቂ ዝግጅት ማድረጉ፣ እንዲሁም ተማሪዎች የፈተና ሥርዓቱን አክብረው በመፈተናቸው ፈተናው በሰላምና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጸዋል።