ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ“የተገልጋይ እርካታ” ዙሪያ ሥልጠና ሰጠ።
ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት “የተገልጋይ እርካታ” በሚል ርዕስ ያተኮረ ሥልጠና አካሂዷል። ሥልጠናው የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻልና የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው እና ከውጭ ተቋማት የተውጣጡ ተሳታፊዎችን አሳትፏል።
በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት የተውጣጡ ተወካዮች፣ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራን እንዲሁም የተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ተሳትፈዋል።
የዕለቱን መርሃ ግብር መምህር ወንድሙ ሐለፎም በማስተዋወቅ ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ተቀብለዋል። በመክፈቻ ንግግራቸው የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር ፅጌ አሰፋ የሥልጠናውን ዓላማ፣ አስፈላጊነት እና በአገልግሎት ማሻሻያ ሂደት ያለውን ሚና በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በመቀጠል የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ረ/ፕሮፌሰር መሰረት መረሳ ስለ “የተገልጋይ እርካታ” ጽንሰ-ሐሳብ፣ አስፈላጊነትና ተቋማዊ ጠቀሜታ አጠቃላይ ግንዛቤና ትንተና አቅርበዋል።
በመቀጠልም ከቱሪዝም ትምህርት ክፍል መምህር አብርሃ ገብረመስቀል እና ከሎጂስቲክስና ሰፕላይ ቼይን ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር ግርማይ ተስፋይ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያና ተግባራዊ ሥልጠና ሰጥተዋል። በሥልጠናውም የተገልጋይ እርካታ ምንነት፣ የአተገባበር ስልቶች፣ ተቋማዊ ጥቅሞች እና በአገልግሎት ጥራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በዝርዝር ተዳስሷል።
በመጨረሻም ተሳታፊዎች ሥልጠናው ጠቃሚና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸው፣ ከቀረቡት ጽንሰ-ሐሳቦችና ተግባራዊ ልምዶች ብዙ እንደተጠቀሙ አስረድተዋል። በተጨማሪም መሰል የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ወደፊትም በቀጣይነት ተጠናክረው እንዲሰጡ ጥያቄና አስተያየታቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም ለሥልጠናው ተሳታፊዎች የተሳትፎ ሰርቲፊኬት የተበረከተ ሲሆን፣ ፕሮግራሙም በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።