ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 2ኛ ዙር ተፈታኞች ኦሬንቴሽን ሰጠ።

ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የ2018 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ማጠናቀቂያ ፈተናን በ2ኛ ዙር ለሚወስዱ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የምረቃ አዳራሽ ገለጻና ኦሬንቴሽን ሰጥቷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ግርማይ ታደለ (ረ/ፕሮፌሰር)፣ ከፌዴራል ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስተባባሪ አቶ ሹሙዬ አበራ፣ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ተወካይ ዶ/ር ዳኘው ገ/ሕይወት፣ እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር መዝገቡ ጋሹ ተገኝተው ተማሪዎቹን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት መልካም የፈተና ጊዜ ተመኝተዋል። በመድረኩ የተናገሩት የግብረ ኃይሉ አባላት፣ ይህ ፈተና ለተማሪዎች ቀጣይ የትምህርት ሕይወታቸውን የሚወስን ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተፈታኞቹ በትኩረትና በራሳቸው ጥረት ፈተናውን በመውሰድ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አበረታተዋል። በኦሬንቴሽኑም ተፈታኞች ፈተናው ከመጀመሩ 30 ደቂቃ በፊት በፈተና ማዕከሉ መገኘት እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ፈተናው ከተጀመረ በኋላ ከ45 ደቂቃ በፊት ከፈተና አዳራሹ መውጣት እንደማይፈቀድ ተገልጿል።