በትግራይ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉበትን ሁኔታና የወደፊት አቅጣጫ የሚገመግም መድረክ ተካሄደ
በትግራይ የሚገኙትን አራቱን ዩኒቨርሲቲዎች፣ ማለትም መቐለ፣ ዓዲግራት፣ አክሱምና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የመማር ማስተማር ሂደት ለማስጀመር ያሉበትን የዝግጅት ደረጃ እና የወደፊት አቅጣጫ ለመገምገም የሚያስችል ውይይት በመቐለ ተካሂዷል።
ውይይቱን የመሩት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የትምህርት ሚኒስትሩ አማካሪ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ሲሆኑ፣ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲዎቹ መደበኛ ሥራቸውን በቶሎ ለመጀመር እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀዋል። አራቱም ተቋማት በቅንጅት፣ በትብብርና በቁርጠኝነት በመሥራት የተማሪዎችን የትምህርት ሂደት ለማስቀጠል እንዲጥሩም አሳስበዋል።
ፕሮፌሰር ክንደያ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ተቋማቱን ለመጠበቅና ለማስቀጠል ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል። በተለይም የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት ያከናወኑት ሥራ በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አድናቆት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገብረምክኤል ወልደገብርኤል በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን ለመጀመር ያለውን የዝግጅት ሁኔታ ከገመገመ በኋላ፣ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማርና ሌሎች መደበኛ ሥራዎቹን ለማከናወን የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት የአራቱም ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች፣ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሌሎች የፌዴራል ተቋማት ሊደረግላቸው ስለሚገባው ድጋፍ ሃሳቦቻቸውን አቅርበዋል። ተቋማቱ የተማሪዎችን ትምህርት ለማስቀጠልና መደበኛ ሥራዎቻቸውን ለማከናወን ያላቸውን ዝግጁነትም አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም፣ አራቱም ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣይ ሥራዎቻቸው ላይ በተከታታይ እየተመካከሩና እየተናበቡ እንዲሠሩ የሚያስችል የጋራ የትብብር መድረክ ለማቋቋም ተስማምተዋል። በዚህም መሠረት፣ በመጪው ሕዳር ወር በራያ ዩኒቨርሲቲ በመገናኘት በጋራ የሚሠሩባቸውን የትብብር አቅጣጫዎች ለመወያየትና ለመድረኩ መነሻ የሚሆን ሃሳብ ለማዘጋጀት ተስማምተዋል።