በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ።

የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ (ዓዩ-ሕጤሳኮ) የ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አካሂዷል።

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር የማነ ገብረማርያም ባቀረቡት ሪፖርት፣ ኮሌጁ በመማርና ማስተማር ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ተመራቂዎችን በማፍራት፣ በጥናትና ምርምር ዘርፍ አሳታፊና ችግር ፈቺ ተግባራትን በማከናወን፣ እንዲሁም በማኅበረሰብ አገልግሎት ተደራሽነትን ማዕከል ባደረጉ ሥራዎች ጉልህ አፈጻጸም እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኮሌጁ ዩኒቨርሲቲው በጤና ዘርፍ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለማሳካት ካስቀመጣቸው ቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያዎች (KPIs) ጋር በተጣጣመ መልኩ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ዶ/ር የማነ እንደገለጹት፣ የዓመቱ ዕቅዶች ከሆስፒታሉ መጠቃለል ጋር በተያያዘ እንደገና ተከልሰው ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም፣ ኮሌጁ በሽግግር ሂደት ላይ በመሆኑ አንዳንድ ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ከቦርድ አመራር ጋር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የግምገማ መድረኩ ዋና ዓላማ በተሰጡ የትኩረት አቅጣጫዎች መሠረት በየዳይሬክቶሬቱ የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም እንደ መልካም ተሞክሮ ሊስፋፉ የሚችሉ አፈጻጸሞችን ለይቶ ለማወቅ፣ እንዲሁም የአፈጻጸም ክፍተት የሚታይባቸውን ዘርፎች በመለየት ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ እንደሚረዳ ዶ/ር የማነ አብራርተዋል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው የ11 ወራት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ከኮሌጁ የማኔጅመንት አባላት፣ ከረዳት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እና ከተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች የተውጣጡ 105 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሚመለከታቸው የማኔጅመንት አባላት ማብራሪያ እና ምላሽ ከተሰጠ በኋላ፣ ሁሉም ሠራተኞች የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ በኃላፊነት እንዲወጡ በማሳሰብ የኮሌጁ ዲን መድረኩን ዘግተዋል።