ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር መከላከል ዙሪያ የግንዛቤና አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጠ።
ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር መከላከል ዙሪያ ያተኮረ የግንዛቤና አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሰጥቷል።
በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች እና የከተማው ማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
መድረኩን የከፈቱት የማህበረሰብ ተሳትፎና ሽግግር አገልግሎት ዳይሬክተር መምህር ፀጌ አሰፋ ሲሆኑ፣ በንግግራቸው የስልጠናውን ዓላማና አስፈላጊነት በማብራራት ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር በግለሰቦችና በማህበረሰብ ላይ የሚያስከትለውን ከባድ ተፅዕኖ አስገንዝበዋል።
ከሕግ ትምህርት ክፍል መምህር ጎይቶኦም ሙዕዝ በበኩላቸው ስለ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ምንነት፣ መንስኤዎች፣ የሕግ ማዕቀፎች እና በሰው ንግድ ዙሪያ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ ሰፊ ማብራሪያና ትንታኔ አቅርበዋል።
በተጨማሪም መምህር ስእለይ ሺለሺ ለችግሩ መንስኤ የሚሆኑ ሁኔታዎችና የመከላከያ ስልቶች ዙሪያ ገለፃ ሰጥተዋል። እንደገለጹት ሥራ አጥነት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ተያያዥ ማህበራዊ ችግሮች ሰዎችን ለሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ተጋላጭ ያደርጋሉ። ችግሩን ለመከላከልም ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በመጨረሻም ተሳታፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን ሃሳቦች በማካፈል፣ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውርን ለመከላከል ሁሉም አካላት በጋራና በተቀናጀ መንገድ መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። በውይይቱም ቀጣይ ሥራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።