የኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የትምህርት ፕሮግራሞች ግምገማ ሪፖርት አቀረበ።
በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ሥር በሚገኙ 10 የመጀመሪያ ዲግሪ (BSc) ፕሮግራሞች ላይ ለአራት ወራት ሲካሄድ የቆየው የትምህርት ፕሮግራም ግምገማ (Academic Program Review) ሪፖርት በዛሬው ዕለት ቀርቧል።
የዕለቱን ፕሮግራም ዶ/ር ሱዑድ ያስተዋወቁ ሲሆን፣ የመክፈቻ ንግግሩን ያደረጉት የኮሌጁ ዲን ረ/ፕሮፌሰር እሱባለው አወቀ ነበሩ።ኮሌጅ ዲኑ በንግግራቸው የፕሮግራም ግምገማ ሥራው በትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው መመሪያ መሠረት ለአራት ወራት በትጋት ሲከናወን መቆየቱን ገልጸው፣ ሪፖርቱ ወደ ግምገማ መድረክ በመድረሱ የሂደቱ አንዱ ወሳኝ ምዕራፍ መጠናቀቁን አስታውቀዋል። በቀጣይም ሁሉም አካላት በትብብር በመሥራት የማሻሻያ ሂደቱን እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።
በመቀጠል የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ረ/ ፕሮፌሰር ግርማይ ታደለ እንደገለጹት፣ የፕሮግራም ግምገማ ሂደቱ ሰፊ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን ጠቁመዋል። እንዲሁም በትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠው መስፈርት መሠረት የሚከናወነው ይህ ግምገማ ፕሮግራሞችን ለመዝጋት ወይም ለመቀነስ ሳይሆን በማሻሻያ ሂደት በኩል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግና ማኅበረሰቡን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚያም ከእያንዳንዱ የትምህርት ክፍል የተወከሉ የኮሌጁ የፕሮግራም ክለሳ ኮሚቴ ኣባላት በየፕሮግራሞቻቸው የተከናወኑ የፕሮግራም ክለሳ ሥራዎችንና ውጤቶቻቸውን በዝርዝር አቅርበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ አካላት ባቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ገንቢ አስተያየቶችና ድጋፍ ሰጪ ሃሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን፣ የተነሱ ጥያቄዎችና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።በመጨረሻም ከመድረኩ በተሰጡ ምላሾችና ማብራሪያዎች ፕሮግራሙ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።
ይህ የፕሮግራም ግምገማ ሂደት በኮሌጁ የሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞችን ጥራት፣ ተዛማጅነትና ውጤታማነት ለማጠናከር የሚያግዝ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑ ተጠቁሟል።