በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ለ3ኛ ዙር ተጠናክሮ ቀጥሏል

የተፈጥሮ አካባቢን ለመጠበቅ፣ የዩኒቨርሲቲውን የአረንጓዴ አሻራ ግብ እውን ለማድረግ እንዲሁም በ3ኛ ዙር የምግብ ዋስትናን ለማጠናከር ያለመው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪዎች በሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገ/ምክኤል ወ/ገብርኤል፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል።

በመርሃ ግብሩ የፍራፍሬ ልማትን ለማስፋፋትና ለምግብ ዋስትና አስተዋጽኦ ለማበርከት ዓላማ ያደረጉ የማንጎ አፕል፣አፕል፣ አበካዶ፣ ግሪፕ ተተክለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገ/ምክኤል ወ/ገብርኤል በመርሃ ግብሩ መጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአንድ ወቅት ዘመቻ ሳይሆን አካባቢን ከጥፋት በመጠበቅ ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢ ለመፍጠር የሚያስችል ዘላቂ አገራዊ ጥረት ነው። በመሆኑም መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ በመንከባከብ የመትረፍ ሁኔታቸውን ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ መጨረሻም በ2017 ዓ.ም. ክረምት የተተከሉ ችግኞች የአካል ምልከታ ተካሂዷል። ምልከታው በቀደሙት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ያሉበትን የእድገትና የጤና ሁኔታ ለመገምገምና ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ ያለውን ሁኔታ ለመለየት ተካሂዷል።

የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ንጉሰ ገብሩ(ተ/ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ የሚተከሉት ችግኞች ዋና ዓላማ የዩኒቨርሲቲውን መልክዓ ምድር ማስዋብና አረንጓዴ ሽፋኑን ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል። ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በዚህ ተግባር ላይ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ በማቅረብ፣ ኮሌጁም ከጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር የተተከሉ ችግኞች በአግባቡ እንዲንከባከቡና እንዲጸድቁ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በቀጣይም የአረንጓዴ አሻራ ልማቱን በማስቀጠል፣ ችግኞችን በአግባቡ በመንከባከብ፣ የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከርና የፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ የዩኒቨርሲቲ ግቢን ለመፍጠር እንዲሁም ለምግብ ዋስትና የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ በቁርጠኝነት ይሠራል።