ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት ከሪሚዲያል ተፈታኝ ተማሪዎች ጋር በተያያዘ የዝግጅትና የማስተባበሪያ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ ከፌዴራል የመጡት የፈተና አስተባባሪ ኣቶ ጥላሁን ደሳለኝ ፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች ተዛማጅ አካላት ተገኝተው ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት ለተፈታኝ ተማሪዎች የሚሰጠው ኦረንቴሽን፣ የፈተና አሰጣጥ ሂደት፣ የፈታኞችና የተፈታኞች ኃላፊነት፣ እንዲሁም የፈተናው ሥነ-ሥርዓት በዝርዝር ተዳሰው ውይይት ተካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገብረሚካኤል ወ/ገብርኤል በበኩላቸው ፈተናው በሰላምና በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ሁሉም አካላት በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የአካዳሚክና ምርምር ም/ፕረዚዳንት ዶ/ር ገብረኪዳን ተስፋይ ስለ ተማሪዎች አጠቃላይ ሁኔታ ገለጻ በማድረግ ለፈተናው የተደረጉ ዝግጅቶችን አቅርበዋል።
በቴክኖሎጂና መረጃ (IT) ዘርፍ የተደረጉ ዝግጅቶችን በተመለከተ የመረጃ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተሩ ነጋሲ ታደሰ በበኩላቸው በፈተናው ሂደት ምንም ዓይነት የቴክኒክ ችግር እንዳይፈጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው የሪሚዲያል ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ አስፈላጊውን የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ እና የሎጂስቲክስ ዝግጅቶች ማጠናቀቁን ገልጿል።